University and City Cooperation

የጅማ ዩኒቨርሲቲና የጅማ ከተማ የግንኙነት ማስተባበርያ ፅ/ቤት

ተቋማችን ጅማ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ዩኒቨርሲቲውን የመሠረቱት ሁለቱ ነባር ተቋማት ማለት የጅማ እርሻ ኮሌጅና የጅማ ጤና ሣይንስ ከተመሰረቱበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ወቅቶች የአካባቢውን ማህበረሰብ ተሣታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደ ነበር ይታወቃል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲም በ1992 ዓ.ም እንደ ዩኒቨርሲቲ በአዋጅ ከተቋቋመ በኃላ የስልጠናና የት/ት ሂደቱን በማህበረሰቡ ተኮር ትምህርትና ስልጠና ፍልስፍና በመቃኘት፤ የመማር ማስተማርና ከጥናትና ምርምር ስራዎች በተጨማሪ ለማህበረሰብ አገልግሎትን ተግባራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፤ ብሎም ፍልስፍና የድህረ-ምርቃና የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ስርዓተ-ትምህርት (curriculum) ውስጥ እንደ መደበኛ የት/ት ዓይነት እንዲካተት ተደርጓል፡፡በዚህም ተማሪዎቻችን በመማርያ ክፍሎች ውስጥ በንድፈሃሣብ የቀሰሙትን ዕውቀት በስራ ላይ እንዲያውሉት የሚያስችል የተግባር ስልጠና ዕድል ከመፍጠሩም በላይ የማህበረሰቡ ችግሮች የሚፈቱበት ሁኔታን አመቻችቷል፡፡
ከመደበኛው የማተትስ ባሻገር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና በመተግበር የማህበረሰቡን ችግሮች በመቅረፍ ብሎም የአካባቢውን ማህበረሰብ የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድም፤በግብርናና በእንስሣት ህክምና፣በጤና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣በትምህርት፤ በሕግ አገልግሎት መስኮች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ፡፡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለሚገኙ መንግስታዊ ተቋማትና ፤ የማህበረሰብ አባላት፤ የፋይናንስ ፤ የሙያና የማቴሪያል፣ ድጋፎችን በስፋት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በጅማ ከተማና በጅማ ዞን ብሎም በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች ላሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን የማህበረሰቡና ለማህበረሰቡ የተፈጠረ ተቋም መሆኑን ያስመሰከረ ተቋምነው፡፡ላለፉት በተከታታይ አምስት ዓመታት በሃገራችን ከሚገኙ የት/ት ተቋማት መካከል በተከታታይነት አንደኛ የመውጣቱ አንዱ ሚስጥርም ይሄው በማህበረሰብ አገልግሎት መስክ ያስመዘገብናቸው አመርቂ ውጤቶች መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
እስካሁን በማህበረሰብ አገልግሎት መስክ ያስመዘገብናቸው ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው ባንድ በኩል ተቋማችን ካስቀመጠው ራዕይና ካለው ተቋማዊ ዓቅም ረገድ በሌላ በኩል ደግሞ በማህበረሰባችን ውስጥ ካለው የትብብር ፍላጐት ስፋትና ባህሪ አኳያ ሰፊ የትብብር መስኮችን መፍጠር፡ የፈጠርናቸውንም የትብብር መስኮችና ተግባራት ይበልጥ ማጠናከርና ማስፋፋት ይጠበቅብናል ፡፡ ይህንንም ስራችንን በደንብ በተደራጀና ራሱን በቻለ ዓብይ ዕቅድ በመመራት ማከናወን ይጠበቅብናል፡፡ ይሄም ዕቅድ ይሄንን ከላይ የተገለጠውን ሐሣብ ከግንዛቤ በማስገባት ፡ የማስተባበርያ ፅ/ቤቱ ሲቋቋም የተቀመጠውን የስራ ድረሻ መሰረት በማድረግ ለመነሻነት የተዘጋጀ ሲሆን፣በየደረጃው ከሚገኙ የሚመለከታቸው የአመራር አካላት ጋር በሚደረግ ውይይት እየዳበረ የሚሔድ ነው፡፡